የልብ ህመምን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል-ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የልብ ህመምን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል-ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2017(ኢዜአ):- የልብ ህመምን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ዜጎች የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንደሚጠበቅባቸው ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ከጤና ተቋማት ጋር በመተባበር "ልብን ለተግባር እናውል" በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፉ የልብ ቀን በአዲስ አበባ አክብሯል።
በኢትዮጵያ ለ9ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25 ጊዜ በተከበረው የልብ ቀን የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ሁኔታና የሕክምና አገልግሎትን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ስኳርና ጨው አብዝቶ መጠቀም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል አለማድረግና ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች የዜጎችን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት ከፍተኛ እንዲሆን እያደረጉት ነው ብለዋል።
የዜጎችን ጤና ለመጠበቅም በቅድመ መከላከል ፖሊሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ዓይነቶችን ተጋላጭነትን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የጤና ምርመራ ባህልን ለማሳደግ በቅርበት የጤና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ፕሬዝደንት እንዳለ ገብሬ፤ የልብ እና የደም ስር ህመሞች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ጫና አሳሳቢነት እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በዚህም ማኅበሩ በአራት የክልል ከተሞች ጭምር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ዜጎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ህብረተሰቡም በኮሊስትሮልና በጉሮሮ ቁስለት የሚከሰትን የልብ ህመም የህክምና ምርመራ በማድረግ ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ተላላፊ ላልሆኑ የበሽታዎች የሚውሉ መድኃኒቶች የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ሐኪም እና የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ደጁማ ያደታ በበኩላቸው በዓለም ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስጋት ጨምሯል።
በተለይ የልብ ህመም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥር አንድ ገዳይ በሽታ በመሆን አሳሳቢነቱ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በለጋ ዕድሜ የሚገኙ ዜጎች ጨምሮ ከጉሮሮ ቁስለት ጋር ተያይዞ በሚከሰት የልብ ህመም ዜጎች ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተጋለጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የልብ ህክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና አገልግሎቱም ያልተስፋፋ በመሆኑ ዜጎች የቅድመ መከላከልና የምርመራ ባህል ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።