በሐረሪ ክልል የኮደርስ ስልጠና በተደራጀ አግባብ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2017(ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል የኮደርስ ስልጠና በተደራጀ አግባብ እየተሰጠ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

የኮደርስ ስልጠና የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማዳበር እንደሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ይፋ የተደረገ የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ መርኃ ግብር ነው።

መርኃ ግብሩ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 5 ሚሊዮን ዜጎችን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።

"ትውልድ ይማር፣ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ታልሞ እየተተገበረ ያለ ፕሮጀክት ነው።

በዚሁ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ዜጎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስልጠናው ዜጎችን በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።

ያለንበት ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን ሲሆን ፤ ወጣቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሳተፍ ለማድረግ ስልጠናው አይተኬ ሚና አለው ብለዋል።

በሐረሪ ክልል በርካታ ወጣቶች የሚገኙ በመሆኑ እነዚህ ወጣቶች የስልጠናው ተሳታፊ እንዲሆኑ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ትምህርት ተቋማት በክረምት ወራት ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በዚህ ስልጠና ላይ እንዲያሳልፉ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል ሁሉም ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ያሉ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ብቁ ሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በአዲሱ በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ስልጠናው የወጣቶችን ቴክኖሎጂ አቅም ከመገንባት ባሻገር ሀገር ለምታደርገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም