የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ኢኮኖሚውን በእውቀት የሚመራ ትውልድ መፍጠር ያስችላል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ኢኮኖሚውን በእውቀት የሚመራ ትውልድ መፍጠር ያስችላል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2017(ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ኢኮኖሚውን በዳበረ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የሚመራ ትውልድ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ሥልጠና የዲጂታል ኢትዮጵያን ስኬት እውን ለማድረግ የተያዘውን ጥረት ለማሳካት እየተሰራ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።
ስልጠናው የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025ን እቅድ እውን በማድረግ የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረውም ይታመናል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኮደርስ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል ነው፡፡
በክልሉ የኮደርስ ስልጠናውን ውጤታማ ለማድረግ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ 65 ሺህ ዜጎችን ለማሰልጠን ክልላዊ አብይ ኮሚቴ አቋቁሞ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
የኮደርስ ስልጠና ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመቀላቀል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የዲጂታል ኢኮኖሚውን በብቃት ለመምራት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
የ5 ሚሊዮን የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ኢኮኖሚውን በዳበረ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የሚመራ ትውልድ መፍጠር ያስችላልም ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችና ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስልጠናውን በመውሰድ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡