ቀጥታ፡

ኢቢሲ በጅማ ከተማ ያስገነባው ስቱዲዮ የአካባቢውን ድንቅ የቱሪዝም ሀብትና ጸጋ ለማስተዋወቅ እድል ይሰጣል

ጅማ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በጅማ ከተማ ያስገነባው ስቱዲዮ በአካባቢው ያለውን ድንቅ የቱሪዝም ሀብትና ጸጋ ለአገሪቷ ሕዝብና ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ እድል ይሰጣል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ ገለጹ።

ኢቢሲ በጅማ ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ ስቱዲዮ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቆ የስርጭት ሥራ ጀምሯል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በጅማ ከተማ ዘመናዊ የቴሌቭዥን ስቱዲዮ መገንባቱ በአካባቢው ያሉትን የቱሪዝም መስህቦችና ሀብቶች ለማስተዋወቅ ያስችላል።

ጅማ በታሪክም፤ በተፈጥሮ ሀብትም እጅግ የላቀ ድርሻ እንዳላት ያመለከቱት አቶ እውነቴ፤ ዘመናዊ ስቱዲዮ መገንባቱ በዚህ በኩል ያለውን ጸጋ ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ኢቢሲ ኢትዮጵያዊያንን እና ምስራቅ አፍሪካዊያንን በመረጃ በማስተሳሰር፤ በዓለም ተደማጭ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "ይህም የይዘት ለውጦች እየተደረጉና ከፍ ያሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያሳያል" ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት የዴሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ ከፍተኛ ሚና በመጫወት አሻራቸውን እያኖሩ ካሉ ሚዲያዎች መካከል አንዱ ኢቢሲ ነው ብለዋል።


 

ተቋሙ የጋራ ትናንትን ብቻ ሳይሆን የጋራን ዛሬ እና ነገን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ቀጣይ ትርክት አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ኢቢሲ ይበልጥ ወደ ህዝብ ወርዶ ለመስራት የጀመረውን ተግባር አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተደራሽ ለመሆን አድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶችና የጋራ እሴቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የጅማ ማህበረሰብም ይህን እድል እንዲጠቀምበት አስገንዝበዋል።

“ኢቢሲ የአካባቢውን የልማት፣ የታሪክና ባህላዊ እሴቶች በማሳየት ተጨማሪ የይዘት ምንጭ ይሆናል።” ያሉት ደግሞ የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።

ዛሬ የተመረቀው የጅማ ስቱዲዮ ከዚህ ቀደም ኢቢሲ በባህር ዳር፣ አሶሳ፣ ሐረር እና ሀዋሳ ካስመረቃቸው በተጨማሪ አምስተኛው የይዘት ምንጭ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው “የስቱዲዮ መቋቋም የጅማን አካባቢ የልማትና የሰላም እሴቶች አጉልቶ ለማሳየት ትልቅ እድል ነው” ብለዋል።

“ኢቢሲ በጅማ ከተማ ስቱዲዮ መክፈቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ክፍል ያሉትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ተከታትሎ ለህዝብ ለማድረስ ትልቅ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው” ሲሉም አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም