ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ ሀገርን የሚጠቅም የልማት ድርጅት ለማድረግ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ ሀገርን የሚጠቅም የልማት ድርጅት ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሀጂ ከማል ሀሩን ገለጹ።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የልማት ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ (ኤሙልኤ) ለውጥን ለማስቀጠል የአመራር ርክክብ አካሂዷል።

የልማት ኤጀንሲው ተጠባባቂ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሱልጣን አህመድ፤ ለአዲሱ ዳይሬክተር አቶ ጁነዲን ሰኢድ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሀጂ ከማል ሀሩን፤ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታውሰው የአሁኑ ለውጥ ለተሻለ አፈፃፀም በማሰብ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው በቀጣይ ህዝበ ሙስሊሙን ብሎም አጠቃላይ ሀገርን የሚጠቅም የልማት ስራ ለማከናወን መዘጋጀቱን አረጋግጠው ለዚህም አዲሱ አመራር በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባልና የትምህርትና ማህበራዊ አገልግሎት ተጠሪ ኢንጅነር አንዋር ሙስጠፋ፤ ኤጀንሲው አሁን ላይ ለአላማው ለመትጋት የሚያስችሉ ለውጦችን ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ አዲሱ አመራር ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ የሚጠበቅበት መሆኑን አንስተው ጠቅላይ ምክር ቤቱን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ ሁሴን፤ የስራ አመራር ቦርዱ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ለውጥ ለማምጣት በመጀመሪያ ፈጣን የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አስታውሰው በቀጣይም ምን መሰራት አለበት ተመላክቷል ብለዋል።

በዚህም መሰረት የአመራር ለውጥ በማድረግ ለተግባራዊነቱ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

 

የቀድሞ የኤጀንሲው ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን አህመድ ስራውን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ አዲስ አመራሮች ወደ ሃላፊነት መምጣታቸው ጥሩ መሆኑን አንስተው በቀጣይ የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

 


 

አዲሱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ጁነዲን ሰኢድ፤ የተሰጣቸውን ትልቅ ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠው ለውጤታማነቱ የሁሉም እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኤጀንሲውን የቆዩ ችግሮች በሂደት በመፍታት ለሀገርና ለህዝበ ሙስሊሙ የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን እንሰራለን ብለዋል።

የመረዳዳት ባህል ግንባታ እንዲሁም መልካም ስብእና ግንባታ ላይ በማተኮርም እንደሚሰራ ጠቅሰው በቂ ፈንድ ለማግኘት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም