ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ የሆኑ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ የሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ፡፡

የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ45ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ "ቱሪዝም የሰላም መሳሪያ"  በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች ዛሬ ተከብሯል።

ቀኑን በማስመልከት በእንጦጦ ፓርክ  የሩጫ እና የጽዳት መርሃ ግብር ተካሄዷል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን፣ መዳረሻዎችን የማልማትና ምቹ የጉብኝት ስፍራ የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለጎብኚዎች ምቹና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን እየገነቡ  መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አነሳሽነት ከተገነቡት መካከል የእንጦጦ ፓርክ፣ አንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች፣ የጎርጎራ፣ ወንጪ እና ጨበራ ጩርጩራ ለአብነት ሲጠቅሱ ሌሎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል ።

የቱሪዝም ዘርፉን የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለማሳደግ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉን አስታውሰው፤ የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ በሀገራቱ መካከል ትስስር የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የቱሪዝም ሻምፒዮን ሆነው መመረጣቸው በቀጣናው ሀገራት መካከል የቱሪዝም መሰረተ ልማት ለማስፋፋት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

የቀኑ መከበር ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ገልጸው ዘንድሮም በተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተከበረ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።

የዓለም የቱሪዝም ቀን እ.አ.አ ከ1980 አንስቶ መስከረም 17 እየተከበረ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም