የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባለፈ የዲፕሎማሲ ስኬትና የቀጣናዊ ትስስር መሰረት እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባለፈ የዲፕሎማሲ ስኬትና የቀጣናዊ ትስስር መሰረት እየሆነ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባለፈ የዲፕሎማሲ ስኬትና የቀጣናዊ ትስስር መሰረት እየሆነ መምጣቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲ ማሀዲ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተጠናከረና በተሳካ መልኩ የቀጠለ የልማት ፕሮግራም መሆኑ ይታወቃል።
በ2015 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተተክለው 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች በተደረገው የዳሰሳ ጥናት 90 በመቶ መጽደቃቸው የታወቀ ሲሆን በተጠናቀቀው ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ የአረንጓዴ አሻራ አርፎበታል።
በዚሁ ሁኔታ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲ ማሀዲ(ዶ/ር) ፤ መርሃ ግብሩ ከሀገራዊ ስኬትም የተሻገረ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባለፈ የዲፕሎማሲና የቀጣናዊ ትስስር መሰረት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በልማት ፕሮግራሙ ሂደት በዘርፉ ከተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራትም ጥሩ አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት በቅጡ የተረዱ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጥቅሙን በመገንዘብ ምስክርነት የሰጡ መሆኑ አንስተዋል።
የጎረቤት አገራትንና ቀጣናውን ጭምር ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ የሰነቀው የልማት ሂደት የጋራ ተጠቃሚነትና የዲፕሎማሲ ስኬት እያመጣ መሆኑንም ዶክተር ፈቲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ቀጣናዊ የልማት ትስስርን የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም በምሳሌነት ሊወስዱት የሚገባ ስኬታማ ከንውን መሆኑን አንስተዋል።
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሳዲግ አደም፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱም ስኬት እየተመዘገበና ተጨባጭ ጠቀሜታም እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ በስኬት መከናወኑ ይታወቃል።