ቀጥታ፡

ኢቢሲ በጅማ ከተማ ያስገነባውን ስቱዲዮ አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ኢቢሲ/ በጅማ ከተማ አዲስ ያስገነባውን ስቱዲዮ አስመረቀ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን "ኢቢሲ ወደ ይዘት" በሚል እያካሄደው ያለው ሪፎርም አካል የሆነው ተጨማሪ የይዘት ምንጭ የኢቢሲ አዲሱ የጅማ ስቱዲዮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኢቢሲ ቦርድ እና ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

አዲሱን ስቱዲዮ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እና የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትጃኒ ናስር በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

ዛሬ የተመረቀው የጅማ ስቱዲዮ ከዚህ ቀደም ኢቢሲ ካስመረቃቸው የባህርዳር፣ አሶሳ፣ ሐረር እና ሀዋሳ በተጨማሪ አምስተኛው የይዘት ምንጭ ነው።


 

በምርቃት ስነ-ስርአቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፣ የኢፌዴሪ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታዎች ሰላማዊት ካሳ እና አቶ ከበደ ዴሲሳ፣ የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጠሀ ቀመር እና ሌሎች እንግዶች መታደማቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም