ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል የምክክር መድረክ ሊያካሂድ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ከመስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ማከናወን እንደሚጀምር አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በሂደቱ በክልሉ ከሚገኙ 49 ወረዳዎች የተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎችን፣ በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማህበራት ወኪሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ከክልሉ የመንግስት አካላት የተወከሉ ተወካዮችን እንደሚያሳትፍ አመልክቷል።

ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ የተጀመረው የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ እስከ አሁን በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳድሮች ሲከናወን ቆይቷል።

በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የጋምቤላ ክልል፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሲዳማ ክልል እና የሐረሪ ክልል ኮሚሽኑ አጀንዳን ያሰባሰበባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ናቸው።

ኮሚሽኑ በቀጣዩቹ ጊዜያት በሶማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና በኦሮሚያ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን ለማከናወን ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም