የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከቀጣናው አገራት ጋር አብሮ መልማትና ማደግን መሰረት ያደረገ ነው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከቀጣናው አገራት ጋር አብሮ መልማትና ማደግን መሰረት ያደረገ ነው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከቀጣናው አገራት ጋር በጋራ መልማትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በሕንድ ውቅያኖስ ያለው የማሪታይም ደህንነት ስጋት እጅጉን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል።
ግጭቶች፣ የባህር ላይ ውንብድናና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት በአካባቢው ያለውን የማሪታይም ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉን አመልክተዋል።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና የማሪታይም ንግድን የምትጠቀመው ኢትዮጵያ በውቅያኖሶቹ ያለውን የማሪታይም ደህንነት በቅርብ እንደምትከታተል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የማሪታይም ደህንነት ጥበቃ ስራዎች ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደር ታዬ የባህር በር የማሰስና የመጠቀም ፍላጎቷ ሊከበር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ከቀጣናው አገራት ጋር በጋራ መልማትና መበልፀግን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነትን በመዋጋት ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በሶማሊያ የሽብርተኛ ቡድን የሆነውን አልሻባብን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማዳከም ረገድ ከሌሎች አገራት ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን አመልክተዋል።
በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት የተገኙ ድሎችን ስጋት ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በሶማሊያ የተገኙ ድሎችን ወደ ኋላ በመመለስ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ሊያስቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም የከፈለችውን መስዋዕትነትና ዋጋ እውቅና ልትሰጥና ልታከብር እንደሚገባም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በተገናኘ የሚቀርቡባትን ክሶችና ወቀሳዎች በፍጹም አትቀበልም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት የሚያግዳት ምንም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ እንዲሁም ለውጤታማ የባለብዙ ወገን የትብብር መድረክ በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።
አምባሳደር ታዬ በንግግራቸው አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንደሚገባት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ጥልቅ ማሻሻያ በማድረግ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ታሪካዊው የትግበራ ምዕራፍ ሊሸጋገር መቃረቡን ገልጸው ይህም በተፋሰሱ አገራት ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ያደርጋል ነው ያሉት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩንና ይህም የኢትዮጵያንና የጎረቤት አገራትን የኤሌትሪክ ኃይል ፍላጎት በመመለስ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ40 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ጠቁመዋል።
አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉንም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት ሰውን ማዕከልና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፤ የዲጂታል መሰረተ ልማት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ የሚያስችሏትን የሞኒተሪና ፊስካል ማሻሻያዎችን እያደረገች እንደምትገኝና ልማትን ማረጋገጥ በሚያስችል ጎዳና ላይ እየተጓዘች መሆኗን አመልክተዋል።
ዓለም አቀፍ አጋር አካላት የኢትዮጵያ የልማት ስራዎች እንዲደግፍም አምባሳደር ታዬ ጥሪ አቅርበዋል።