ኢትዮጵያ እና ኩባ በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኩባ በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኩባ ያላቸውን የባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር አየለ ሊሬ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አሌሃንድሮ ሲማንካስ እና ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ዳይሬክተር ሉዊስ አልቤርቶ አሞሮስ ኑኔዝ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያና በኩባ መካከል ያለውን ታሪካዊና መልካም ግንኙነት በማውሳት፣ የሁለቱ አገራት ትብብሮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
በተለይ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ወደ ትግበራ እንዲሸጋገሩ ክትትል ለማድረግና አዳዲስ የትብብር ዘርፎችን ለመመልከት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች አምባሳደር አየለ በኩባ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለትዮሽ ትብብሩን ለማጠናከር ለሚያከናውኗቸው ስራዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት ያላቸውን የባለ ብዙ ወገን መድረኮች ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ኩባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1975 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።