ቀጥታ፡

ኮሩ የፅንፈኛውን ቡድን ሴሎች ለመበጣጠስ ባካሄደው ዘመቻ በርካቶችን በቁጥጥር ስር አዋለ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2017(ኢዜአ)፦ ኮሩ የፅንፈኛውን ሴሎች ለመበጣጠስ ባካሄደው ዘመቻ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

በምዕራብ ዕዝ የአንድ ኮር አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል አዘዘው መኮንን ኮሩ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና በየከተማው ተሰግስገው የነበሩ የፅንፈኛው ቡድን ሴሎች በመረጃና በህብረተሰቡ ጥቆማ በመለየት በተጠና መንገድ ባካሄደው አሰሳ በበረሃውና በከተማው ፅንፈኛ መካከል የነበረውን የግንኙነት ኔትወርክ መበጣጠስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ብቸና፣ ሸበል፣መርጦለማርያምና ግንደወይን ከተሞች ላይ የፅንፈኛው ቡድን ሰርጎ በመግባት ትምህርት እንዳይጀመር፣አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራቸውን እንዳይሰሩ በማያልቀው የውሸት ፕሮፖጋንዳቸው ህዝብን ሲያደናግሩ በነበሩት ላይ ጠንከር ያለ አርምጃ መወሰዱንም አዛዡ ተናግረዋል።


 

ብርጋዲየር ጄኔራል አዘዘው መኮንን በጥንቃቄና ዘዴ በተሞላበት አግባብ በተደረገው ኦፕሬሽን የተገኘው ውጤት የጥፋት ቡድኖች የትም እንደማይደርሱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በተደረገ አሰሳና ፍተሻ ከፅንኛው ሴሎች፣ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች፣ያለ ህጋዊ ፍቃድ የጦር መሳሪያ ታጣቂዎች 101 ክላሽ፣73ሽጉጥ፣10 ኋላቀር፣04 ቦምብ፣188 የክላሽ ካዝና፣20 ገጀራ፣16 የወገብ ትጥቅና

3667 የተለያዩ መሳሪያ ተተኳሾች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ብርጋዲየር ጀኔራል አዘዘው መኮንን ገልፀዋል።

በህገ ወጥ ተግባራት የተሳተፉ 67 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉንና ከ40 በላይ የፅንፈኛው ቡድን አባላት የነበሩ በራሳቸው ፍቃድ ለሰራዊቱ እጅ መስጠታቸውን አዛዡ መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም