ቀጥታ፡

አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘቷ ጉዳይ ላይ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆናለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2017(ኢዜአ):- 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒውዮርክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

“ማንንም ወደ ኋላ አለማስቀረት ለአሁኑና ለመጭው ትውልድ ሰላም ዘላቂ ልማትና ሰብዓዊ ክብር በጋራ መሥራት" የጉባኤው መሪ ቃልና ጭብጥ ነው።

በግዙፉና በጉምቱው የዓለም የብዝሃወገን ዲፕሎማሲ መድረክ ከሰላም እስከ አየር ንብረት ለውጥ፣ ከዘላቂ ልማት እስከ ዲጂታል አካታችነት፣ ከሰብዓዊነት እስከ የዓለም የኢኮኖሚ አወቃቀር፣ በዓለም መድረክ ፍትሐዊ ውክልናን ከማግኘት እስከ ዓለም በቀጣይ ምን ትሆን? ድረስ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ውይይቶችና ክርክሮች በማድረግ ለወደፊቱ ይበጃሉ የተባሉ ሀሳቦች በመነሳት ላይ ይገኛሉ።

በጠቅላላ ጉባኤው ጎልተው ከተሰሙ አንኳር ጉዳዮች መካከል አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለው የረጅም ጊዜ ጥያቄ ይገኝበታል።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች አፍሪካ በምክር ቤቱ ሁለት ቋሚ መቀመጫና ድምጽን በድምጽ የመሻር ኃይል ሊሰጣት ይገባል በሚለው ጉዳይ የጋራ አቋም ይዘዋል።

ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ አለማግኘቷ ፍትሐዊ አይደለም በማለት እየሞገቱ ይገኛል።

በተለይም ከ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ በሆነው የመጪው ጊዜ ጉባዔ (Summit of the Future) አጀንዳው በስፋት ተነስቷል።

የዛምቢያ የመሰረተ ልማት፣ ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትር ቻርልስ ሚሉፒ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ማግኘት አለባት የሚለው መልዕክት ይበልጥ ከፍ ብሎ እየተሰማና ለሚመለከተው ሁሉ እየደረሰ እንደሚገኝ ለቲአርቲ ገልጸዋል።

አፍሪካ በተመድ ውስጥ ፍትሐዊ ውክልና ያስፈልጋታል፣ ቋሚ የፀጥታው ምክር ቤት አገራት ምክር ቤቱ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የናምቢያ ቋሚ መልዕክተኛ ፔንዳ ናንዳ ከቋሚ መቀመጫ ባለፈ አፍሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ሊኖራት ይገባል፣ በዓለም ጉዳዮች ላይ መወሰን ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

የጋና የጤና ሚኒስትር በርናርድ ኦኮ ቦዬ በጠቅላላ ጉባኤው አፍሪካ በተመድ ያላት ኢ-ፍትሐዊ እና ነባራዊ እውነታን ያላገነዘበ ውክልና መቀየር አለባት የሚለው አጀንዳ የቅድሚያ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል።

አፍሪካውያን አንድ ስንሆን ተደማጭ እንሆናለን በአንድነት መቆማችን በዓለም መድረክ ይበልጥ ትኩረት እንድናገኝ አድርጎናል ብለዋል።

አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ከማግኘቷ ባለፈ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን ማግኘቷ በራሷ የመወሰንን አቅም የማሳደግና የአህጉሪቷ ፍላጎቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት 54 አገራትና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላትን አፍሪካን አለማካተቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

የተወሰኑ አካላት በአብዛኛው ዕጣ ፈንታ ላይ የሚወስኑበት አካሄድ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የማላዊ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ለአፍሪካ ሁለት ቋሚ መቀመጫና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት በመስጠት ለዴሞክራሲ መስፈን ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።

የበለፀጉ አገራት የአፍሪካን ጥያቄ ተቀብለው ድጋፋቸውን መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አፍሪካውያን በጠቅላላ ጉባኤው በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘቷ ጉዳይ ላይ አንድ መሆናቸውን እንዳሳዩም የቲአርቲ ዘገባ ያመለክታል።

79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም