ቀጥታ፡

ምዕመናንና አገልጋዮች የሚናፈቁት  ዓመታዊ ክብረ በዓል - መስቀል

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ክብረ በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለያየ ክዋኔዎች በድምቀት ይከበራል። 

ከሃይማኖታዊ አንድምታው ባሻገር በየአካባቢው የሚስተዋሉ የመስቀል ክብረ በዓል ማህበራዊና ባህላዊ ክዋኔዎችም በምዕመናን ዘንድ ይናፈቃሉ። 

በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የሚከበረውን የደመራ በዓልም ምዕመናንም ሆነ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በጉጉት ይጠብቁታል። 

መስቀል ባህላችንን የሚያንጸባርቅ የብርሀን ቀን ነው የሚሉት የበዓሉ ታዳሚ ለገሰ አለማየሁ፤ መስቀልን በየዓመቱ በመስቀል አደባባይ በመገኘት ያከብሩታል። 

ምዕመናንን፣ ሰንበት ተማሪዎችና፣ የሀይማኖት አባቶች ጸአዳ በመልበስ የመስቀል በዓልን የብርሃን ተምሳሌትነት የሚያሳዩበት መሆኑን ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ ከልጅነታቸው ጀምሮ በየዓመቱ ወደ መስቀል አደባባይ በማምራት በአገልግሎትም ሆነ በታዳሚነት


 

የሚያከብሩት ሊዲያ ዝቄ መስቀል ለመስቀል ልዩ ስሜት አላቸው።

የመስቀል ደመራ በዓል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታው ይበልጥ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ።  


 

የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑት አብርሃም አጥላውና ሀብቶም ሰለሞን ከገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ትምህርት ቤት ከልጅነታቸው ጀምሮ ለደመራ ክዋኔዎች ሲያገለግሉ ኖረዋል። 

የመስቀል በዓል የተለያዩ አድባራት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ ዝማሬዎችን እያጠኑ ዝግጅት የሚያደርጉት እንዲሁም አብሮ አደጎችና ቤተሰባዊያን በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ ማህበራዊ ገጽታውን በጣም ይናፍቁታል።

የመስቀል ደመራ በዓል ጥንታዊ እና ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናት ማመስገኛ እና መገልገያ ንዋየ ቅድሳት በአደባባይ ጎልተው የሚታዩበት ነው። 

ከነዚህም መካከል ምዕመናን ደምቀው የሚታዩባቸው አልባሳትን ጨምሮ እንደ ጽናጽል፣ መቋሚያ፣ ከበሮ፣ መለከት ያሉ የዝማሬ መሳሪያዎች ከክብረ በዓሉ ውብ መልኮች መካከል ይጠቀሳሉ።


 

መስፍን ንጉሴ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው በየዓመቱ ጥንግ  ደርበው፤ ጽናጽል እና መቋሚያ ጨብጠው በወረብና ዝማሬ ያገለግላሉ።

እነዚህ የመገልገያ መሳሪያዎች የራሳቸው መንፈሳዊ ትዕምርትና እሴቶች ያላቸው መሆኑን ይገልጻሉ። 


 

ዘካሪያስ ዘላለም እና መሰል ወጣቶችም በአዘቦት የማይዘወተረውን የመለከት የትንፋሽ መሳሪያ በመያዝ በአንድነት ክብረ በዓሉን ያደምቃሉ፤ አገልግሎታቸውንም ሰርክ ይጓጉለታል።

የመስቀል ደመራ በዓል እ.አ.አ በ2013 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ደግሞ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ መልክ እንዲኖረው ማድረጉንም  ነው ምዕመናኑና አገልጋዮቹ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም