የኮደርስ ሥልጠና በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ በማፍራት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ሥልጠና በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ በማፍራት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2017(ኢዜአ):- የኮደርስ ሥልጠና በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ በማፍራት ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።
የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገ የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ መርኃ ግብር ነው።
መርኃ ግብሩ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 5 ሚሊዮን ዜጎችን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።
"ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ታልሞ እየተተገበረ ያለ ፕሮጀክት ነው።
በዚሁ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ዜጎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስልጠናው በቴክኖሎጂ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የዜጎችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም በማጎልበት የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ በማፋጠን ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የግብይት ስርዓት ወደ ዲጂታል አገልግሎት እየተቀየረ መሆኑን በመግለፅ፤ በዚህ አገልግሎት ለመስጠትና ተጠቃሚ ለመሆን ኮደረስ ስልጠናውን መውስድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና በክልሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እንዲሳተፉ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ በሰፊው መሰራቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ዜጎች በስልጠናው በመሳተፍ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ በመፍጠር ስልጠናው መጀመሩን አስረድተዋል።
ስልጠናው ዜጎች በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና የሀገርን እድገት ለማሳለጥ የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዜጎችም ይህንን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ስልጠና በመውሰድ ራሳቸውን፣ ሀገራቸውና ህዝባቸውን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።