የኮደርስ ስልጠና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት በብቃት እንድትወጣ ያግዛታል - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ስልጠና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት በብቃት እንድትወጣ ያግዛታል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2017(ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ፣ በጸጥታና በቴክኖሎጂ የምታደርገውን ውድድር በብቃት እንድትወጣ እንደሚያግዛት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የሆነው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና በመላ ሀገሪቱ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ስልጠናውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኮደርስ ስልጠና በክልሉ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ለኮሌጅ እና ለዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች እንዲሁም ማንበብና መጻፍ ለሚችሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት በማዳበር አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለንበት የውድድር ዓለም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ማፍራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ፈጣን እድገት ለማምጣት ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድ ነድፋ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ስታደርግ መቆየቷል አንስተዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባከናወነቻቸው ተግባራት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል፡፡
በመተግበር ላይ ያለው ኮደርስ ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ፣ በጸጥታና በቴክኖሎጅ ዘርፎች የመወዳደር አቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡
የኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ከጠባቂነት ወደ ስራ ፈጠሪነት እንዲሸጋገሩ የሚያግዝ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ስልጠናው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በይፋ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በተፈጠረው ዕድል በመመዝገብ በልዩ ትኩረት መከታተልና መሰልጠን እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ሁሉም በስልጠናው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።