የመስቀል በዓል ሲከበር በመስቀሉ ላይ የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ ሰላምና ፍቅር ለማጽናት በመትጋት መሆን አለበት --- ብፅዑ አቡነ ሰላማ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል ሲከበር በመስቀሉ ላይ የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ ሰላምና ፍቅር ለማጽናት በመትጋት መሆን አለበት --- ብፅዑ አቡነ ሰላማ

ባህር ዳር፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):- የመስቀል በዓል ሲከበር በመስቀሉ ላይ የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ ሰላምና ፍቅር ለመጽናት በመትጋት መሆን እንዳለበት የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በፅዕ አቡነ ሰላማ ገለጹ።
የደመራ በዓል የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ በድምቀት ተክብሯል።
ብፅዑ አቡነ ሰላማ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምዕመኑ የመስቀልን በዓል ሲያከብር በመስቀሉ ላይ የተከፈለውን ዋጋ፣ ዓላማና የተገኘውን ጸጋ በመጠበቅ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
መስቀል እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሰላምና ፍቅር ሲል ዋጋ የከፈለበት ምልክት መሆኑን አውስተው፤ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር እርስ በእርሱ በመፈቃቀርና አንድነቱን በማጠናከር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ያስቻለው በአካባቢው ሰላም በመኖሩ ነው።
ለዚህም የጸጥታ ሃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊመሰገኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ በመቀጠል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።