የመስቀል በዓልን ስናከብር የተቸገሩትን ወገኖች በመደገፍ እና በመርዳት መሆን ይገባል - ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓልን ስናከብር የተቸገሩትን ወገኖች በመደገፍ እና በመርዳት መሆን ይገባል - ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ
ድሬዳዋ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):- የመስቀል በዓልን ስናከብር የተቸገሩትን ወገኖች በመደገፍ እና በመርዳት መሆን እንደሚገባ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ገለጹ።
በድሬዳዋ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች በተገኙበት የደመራ በዓል በድምቀት ተከብሯል።
በድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ የተዘጋጀውን ደመራ ማምሻውን የለኮሱት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ በበዓሉ ላይ ለተገኙ ህዝበ ክርስቲያን አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው በዓሉን በመደጋገፍና በመረዳዳት ማክበር እንደሚገባ አስታውሰው፤ ፈጣሪ የኢትዮጵያን ህዝብ ጠብቆ ለመጪው ዘመን እንዲያደርስ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
ለመላው የበዓሉ አክባሪዎችም የእንኳን አደረሳቹሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ገበየሁ ጥላሁን የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊ እሴቶቹ ባሻገር የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ማህበራዊ እሴቶቹ የሚደምቁበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን ወገኖች በመደገፍ እና በመርዳት መሆን እንደሚገባም አቶ ገበየሁ ገልጸዋል።