ቀጥታ፡

መስቀል የመቻቻልና የህብረት ምልክት በመሆኑ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር አንድነቱንና አብሮነቱን በማጎልበት መሆን አለበት -- ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ

አዳማ/ነጌሌ፤መስከረም 16/2017( ኢዜአ)፡-..መስቀል የመቻቻልና የህብረት ምልክት በመሆኑ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር አንድነቱንና አብሮነቱን በማጎልበት መሆን እንዳለበት የምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጰጰስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ አስገነዘቡ።

የመስቀል ደመራ በዓል በአዳማ ከተማ እና በምስራቅ ቦረና ዞን ነጌሌ ቦረና ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት መስቀል የአብሮነት፣ መቻቻልና ህብረት የሚታይበት ሀይማኖታዊ የአደባባይ በዓል ነው።


 

''እንደዚህ አይነት ሀይማኖታዊ በዓላትንም ማክበር የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ትውልዱ ከአባቶች የተረከበውን አንድነትና ህብረት በማጠናከር ለሀገሩ ሰላም ዘብ በመቆም መሆን አለበት'' ብለዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሙላቱ ዲባ በበኩላቸው አዳማ የመቻቻል፣ የአብሮነትና አንድነት ተምሳሌት ከተማ ናት ብለዋል።

''የሰላማችን ምስጢር አብሮነታችንና አንድነታችን ነው'' ያሉት ምክትል ከንቲባው ''መላው የከተማዋ ነዋሪ የሰላም ባለቤትነቱን ይበልጥ በማጠናከር ልማትን ማፋጠን አለበት'' ሲሉም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ የደመራ በዓል በምስራቅ ቦረና ዞን ነጌሌ ቦረና ከተማ የሀይማኖት አባቶችና ምዕመናን እንዲሁም የዞኑ ከፍተኛ አመራር አባላት በተገኙበት ተከብሯል።

በዚሁ ጊዜ ሰላምን ለማጽናት ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ የገለጹት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊበን፣ ጉጂና ቦረና ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን ጥበቡ ጸጋዬ ናቸው።

በአሉ የደመቀ እንዲሆን የመንግስት አመራርን ጨምሮ የሌሎች ሀይማኖት ተከታዮችም በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ በማጽዳትጭምር መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

''ደመራን ተባብረን እንዳከበርን ሁሉ አንድ ሆነን ለሰላም፣ ለልማትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ልንተባበርና በጋራ ልንቆም ይገባል'' ብለዋል።

የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን፣ በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል በአል የሁሉም በአል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

''አባቶቻችን ያቆዩልንን የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የመተባበር እሴቶችን ልንጠብቃቸው ይገባል'' ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ''የዞኑ ህዝብ አካባቢውን በመጠበቅ ከመንግስት ጎን መቆም አለበት'' ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም