የመስቀል በዓል በሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት የሚገለጽበት የጋራ እሴት ነው - ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል በሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት የሚገለጽበት የጋራ እሴት ነው - ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):- የመስቀል በዓል በሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት የሚገለጽበት የጋራ በዓልና እሴት መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ባህልና ቅርስ ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የሰፈረው የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የእምነቱ ተከታዮችና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ ኢትዮጵያ በበርካታ መዛግብታዊ ማስረጃ ከዓለም ቀዳሚ እና የገዘፈ የታሪክ ባለቤት የሆነች ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ዘንድ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው የግዙፍ እሴት ባለቤት መሆኗን በመጥቀስ ለዚህ ማሳያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚገኙ ዕንቁ እሴቶች መካከል የመስቀል በዓል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የመስቀል ደመራ በዓልም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ባህልና ቅርስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ዕውቅናን የተቸረው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵዊያን ድንቅ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ በመላ ኢትዮጵያ ከሚከበሩ በዓላት አንዱና ድንቅ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓተ ትውፊቶች የሚገለጹበት ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ ዋነኛ ባህላችን ነው ብለዋል።
ሥነ-ስርዓቱ ፍቅር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ መተሳሰብና መረዳዳት የሚገለጽበት እንዲሁም ዜጎችን የሚያቀራርብ ድንቅ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል።
መስቀል ፍቅር ነው፣ መስቀል እየሱስ ክርስቶስ ያለአንዳች ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ህይውቱን በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን የገለጸበት በዓል ስለመሆኑም አንስተዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓል ባህላዊ ትዕይንትና ሕብረብሔራዊ አንድነትና አብሮነት ጎልተው የሚታዩበት የጋራ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠፍቶ ተደብቆና ተቀብሮ የነበረው መስቀል ከተደበቀበት ስፍራ የወጣበትን ቀን በውብ ኃይማኖታዊ ሥርዓት በማክበር የመስቀሉን መገኘትና ተቀብሮ አለመቅረት በማብሰር ግማደ መስቀሉን ይዛና ጠብቃ በማኖሯ እንኮራባታለን ብለዋል።
መስቀል የአብሮነት የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር ምልክት በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሙሉ ልብ መነሳሳትና ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብርቅየና ባህላዊ እሴቶች እንዲለሙ፣ እንዲጠበቁና ለትውልድ እንዲሻገሩ ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።