ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ መገለጫነቱን፣ ባህላዊ ትውፊቱንና ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል - የኃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017 (ኢዜአ)፦ የሰላም ምልክት የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ መገለጫነቱን፣ ባህላዊ ትውፊቱንና ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

መርኃ-ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ የእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም ዲፕሎማቶችና ጎብኚዎች ተገኝተዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ከተገኙት ኢዜአ ካነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች መካከል ሊቀ ሊቃውንት የኋላወርቅ ኃይለሥላሴ  እና ሊቀ ብርሃናት በሐታ ተክለወልድ፤ የመስቀል በዓል ከኃይማኖት መገለጫነቱ ባሻገር የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ኃብት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የሰላም ምልክት የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ መገለጫነቱን፣ ባህላዊ ትውፊቱንና ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል ብለዋል።


 

በዓሉን ስናከብር በመስቀሉ የተገለጠውን የክርስቶስ ቤዛነት፣ ፍቅር እና እውነትነት አርዓያ በመከተል መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የአንድነት፣ የአብሮነትና የጽናት ማሳያ የሆነውን በዓል በመዋደድ ልዩነትን፣ መራራቅን እና አለመግባባትን በማስወገድ አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

በመሆኑም የአብሮነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫና የጋራ ኃብት የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል  እሴቱን ጠብቆ ማክበርና ለትውልድ ማቆየት ይገባል ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም