የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለመስቀል ደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለመስቀል ደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለ2017 የመስቀል ደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
ከብዙ ፍለጋ እና ድካም በኋላ የተገኘው ቅዱስ መስቀል ከኃጢአት ጥላ፣ ከጥፋት ጨለማ የወጣንበት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት የነፍሳችን ብርሃን፣ የሕይወታችን መብራት ነው።
የመስቀል ደመራ በዓል በሃይማኖትም ሆነ በባህላዊ ትዉፊቱ ትልቅ አስተምህሮት አለዉ። ከበረቱ፣ ከታገሉ እና ከጸኑ የማይሳካ ነገር እንደሌለ፤ የጸና የድል ባለቤት እንደሚሆን ከመስቀል ደመራ እንማራለን፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ ለሚተጉ እንደ ንግሥት እሌኒ ሕልሙ እውን ሆኖ ማየቱ አይቀርም፡፡ ደመራ ከተለያዩ አካባቢዎች ተውጣጥተው በተሠበሠቡ ችቦዎች ተደምሮ ብርሃን ይሰጣል፤ ይህ የሚያስተምረው አንድነትን፣ ኅብረትን፣ ፍቅርን እና መረዳዳትን ነው።
እኛም በሚገጥሙን ፈተናዎች ሁሉ ሳንንበረከክ እንደ ደመራዉ በአንድነት ከቆምን አሁን ካለንበት ፈተናዎች ሁሉ አልፈን ከደመራዉ ብርሃን ማግስት የድካማችንን ውጤት ማየት እንደምንጀምር በማመን እንዲሁም የመስቀል ደመራ በዓልን ተሰባስበን ስናከብር ጠፍቶ የቆየውን አንድነትና መሰባሰብን በማሰብ ብርሃኑ ጨለማውን እንደሚያጠፋዉ ሁሉ እኛም በፍቅር አንድ ሆነንና ተሰባስበን ከሰራን ጠንካራ፣ የበለፀገች፣ ዘላቂ ሰላሟ እና አንድነቷ የፀና ህብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ማየታችን አይቀርም።
ለመስቀሉ ክብር ስንሰጥና፣ የደመራውን በዓል ስናከብር መስቀል የትዕግሥት፣ የዕርቅና የሰላም ምልክት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። በመስቀሉ የተደረገው ዕርቅና፣ የተገኘው ሰላም በሁላችን ልብ መገኘት ይኖርበታል። ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ያገኘችው በእምነት ፅናት፣ በብዙ ፍለጋ፣ ትዕግሥትና፣ ድካም ነው። እኛም ለትጋታችን መልስ፣ ለፍለጋችን ምልክት እስከምናገኝ በጽናት መስራት ይኖርብናል።
ስለሆነም አንድነታችን ፍፁም በሆነ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ላይ በመገንባት እንደ ደመራችን ብርሃን ተስፋችንን እናድምቅ ፤ በአንድነት ተሰባስበን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንሻገር።