በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ መልካም ዕድል የፈጠረ ነው - ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የጠዴ ዲልዲማ ቀበሌ አስተዳደርን ጎብኝተዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አዲስ የቀበሌና የወረዳ መዋቅር አደረጃጀት ወደ ስራ ማስገባቱ ይታወቃል። 

በክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ልዑክ በዛሬው ዕለት በምስራቅ ሸዋ ዞን እንደ አዲስ የተዋቀረውን የጠዴ ዲልዲማ ቀበሌ የስራ ሁኔታ ተመልክተዋል። 

ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ለህዝቡ በቅርበት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል። 

ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት፤ በቀበሌ ደረጃ የተመደቡት አመራሮች ለህዝቡ ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት መስጠት አለባቸው ብለዋል።

አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ሰላምን ለማስፈን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቅርበት ምላሽ ለመስጠት የቀበሌ አመራር ቁርጠኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ 

በኦሮሚያ በክልል ደረጃ በተዋቀሩ የቀበሌ አደረጃጃቶች ውስጥ ከ50 ሺሀ በላይ ባለሙያዎች ለህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል።   

የጠዴ ዲልዲማ ቀበሌ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ትዕግስት ኢብራሂም አደረጃጀቱ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

የተመደቡት አመራሮች ዝቅ ብለው ህዝቡን ለማገልገል እና ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጠዴ ዲልዲማ ቀበሌ ነዋሪዎች መንግስት በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም ጉዳዮቻቸውን ለማስፈጸም ወደ ወረዳና ዞን ይመላለሱ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ አደረጃጀቱ እንግልታቸውን እንደሚቀንስላቸው ተናግረዋል፡፡

አመራሮቹ የያዙት ዕቅድና የህዝቡ ተጠቃሚነት ተግባራዊ እንዲሆን በቅርበት እንደሚደግፉም ጠቁመዋል፡፡

የምስራቅ ሸዋ ዞን በ302 የቀበሌ አስተዳደር የተደራጀ ሲሆን 281 የሚሆኑት የቀበሌ አስተዳደሮች ወደ ስራ ገብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው በዚሁ ወቅት ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም