የደመራና የመስቀል በዓል ሲከበር ከመስቀሉ አብነት የተገኘውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል--ብፁዓን አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የደመራና የመስቀል በዓል ሲከበር ከመስቀሉ አብነት የተገኘውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል--ብፁዓን አባቶች
ጎንደር/ሐረር/ባህር ዳር፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፡-የደመራና የመስቀል በዓል ሲከበር ከመስቀሉ አብነት የተገኘውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ የምስራቅ ሐረርጌ እና የባህር ዳር ሐገረ ስብከቶች አስታወቁ።
የሀገረ ስብከቶቹ ብጹዓነ አባቶች በዓሉን በፍቅርና በጎ ሥራ በመፈጸም ማክበር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ለእምነቱ ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ሰላም ነው።
"ሰላም ከሌለ አቅመ ደካሞች ብቻ ሳይሆኑ አቅም ያላቸውም እንደ ልብ መንቀሳቀስ አይችሉም" ያሉት ብጹዕነታቸው፤ ለዚህም አዲሱን ዘመን ለሰላምና ለአንድነት መጠቀም ይገባል ብለዋል።
"መስቀሉ ከፈጣሪያችን ጋር የታረቅንበትና ሰላምን ያገኘንበት ነው" ያሉት ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ፣ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የሃይማኖቱን አስተምህሮዎች በመተግበር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
በመስቀሉ አብነት የተገኘውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ከማጠናከር ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማሰብ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለዘላቂ ሰላም ጠንክረው እንዲሰሩም ብጹዕነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ምዕመኑ የደመራና የመስቀል በዓልን ሲያከብር አንድነቱን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ በዓሉን አስመልክተው እንደገለጹት መስቀል የአብሮነት፣ የአንድነትና የፍቅር መገለጫ በዓል ነው።
መስቀሉ ጥላቻ የተወገደበትና ፍቅርና አንድነት የሰፈነበት በመሆኑ ምዕመኑ በዓሉን ሰላሙንና አብሮነቱን በሚያጠናከር መልኩ ማክበር እንዳለበት ተናግረዋል።
መስቀል ክርስቶስ ለእኛ ሲል ፍቅርን በተግባር ያሳየበትና ሰላምን ለሰው ልጆች የሰጠበት በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሰላምና በጋራ እንዲያከበር አስገንዝበዋል።
"ክርስቶስ የሞተውና የተሰቀለው ለሁሉም ነው፤ እናም ምዕመኑ በዓሉን የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በማጉረስና የተቸገሩትን በመርዳት በአብሮነት ማክበር አለባቸው" ብለዋል።
ምዕመኑ ወደ ለደመራ በዓል ሲመጣም ፍቅርና አብሮነትን በማጽናት መሆን አለበት ሲሉም ነው ብፁዕነታቸው የተናገሩት።
የመስቀል ደመራ በዓል ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንም ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ተመኝተዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላምና በአብሮነት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የገለጸው ደግሞ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ነው።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊና ተወካይ ሥራ አስኪያጅ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን እንዳሉት፣ የመስቀል ደመራ በዓል የፍቅርና የመተሳሰብ በዓል ነው።
በባህር ዳር ከተማ ዛሬ የሚከበረው የደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበርም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በተለይም መስቀልን ስናከብር በየሆስፒታሉ የተኙ ህሙማንን እንዲሁም ከቤታቸውና ከመኖሪያ ቄያቸው የተፈናቀሉትን በመጠየቅ፣ በጎ ሥራ በመፈጸምና በመተሳሰብ መሆን አለብት ብለዋል።