ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር አረቦን ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር አረቦን ለመሰብሰብ መታቀዱን የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ገለጸ።

የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር)፤ የ2016 ዓ.ም እና የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና ዝግጅት በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከአባል ፋይናንስ ተቋማት አረቦን መሰብሰብ፣ የተሰበሰበን አረቦን በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ኢንቨስት ማድረግና አንድ የፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ ተቋሙን በመተካት ለገንዘብ አስቀማጮች መክፈል ከዋና ዋና ተግባራቱ መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የግል ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አባል መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በዚህም እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የመድን ሽፋን በመስጠት ከ100 ሺህ ብር በታች ተቀማጭ ገንዘብ ላለው ግለሰብና ድርጅት ፈንዱ ሙሉ በሙሉ ገንዘቡን ተመላሽ የሚያደርግለት መሆኑን ተናግረዋል።

ከ100 ሺህ ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ላለው ግለሰብና ድርጅትም እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ፈንዱን ተመላሽ በማድረግ ቀሪውን ገንዘብ በወደቀው የፋይናንስ ተቋም ተጣርቶ ተመላሽ ሊደረግ እንደሚችል አስረድተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ተቋማዊ መዋቅርና አደረጃጀት፣ የመመሪያና የሥራ ማስኬጃ በጀት ዝግጅት እንዲሁም አጋዥ የሆኑ የሥራ መግባቢያ ስምምነት መደረጋቸውን አንስተዋል።

ከፈንዱ አባል የፋይናንስ ተቋማት 6 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር አረቦን በመሰብሰብ 6 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር ኢንቨስት ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

የ5 ነጥብ 94 ቢሊየን ብሩ በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ኢንቨስት ተደርጓል፤ ቀሪ 539 ነጥብ 64 ሚሊየን ብር ደግሞ በሸሪዓ መርህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙዳራባህ ኢንቨስትመንት ሒሳብ ተቀምጧል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመትም 86 ከሚሆኑ የአባል ፋይናንስ ተቋማት 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር አረቦን ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተሰበሰበውን አረቦን በአግባቡ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል የማስተዳደር አቅሙን ለማሳደግና ለጤናማ የፋይናንስ ተቋማት ተወዳዳሪነት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ 31 ባንኮችን እና 55 ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በአባልነት በመያዝ ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሆኑ ይታወቃል።

ከአባል የፋይናንስ ተቋማት አማካይ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 0 ነጥብ 3 በመቶ አረቦን የሚሰበስብ ሲሆን፤ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና ከማይክሮ ፋይናንስ ማኅበር በተውጣጡ የቦርድ ኃላፊዎች በደንብ ቁጥር 482/2013 የሚመራ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም