ቀጥታ፡

የ "ጋሪ ዎሮ" በዓል በተለያዩ አካባቢዎች መከበሩ የብሔረሰቡ ማንነት እና እሴቶች እንዲተዋወቁ አድርጓል - የብሔረሰቡ ተወላጆች

አሶሳ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፦ የቦሮ ሽናሻ የዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" በተለያዩ አካባቢዎች መከበሩ የብሔረሰቡ ማንነት እና እሴቶች እንዲተዋወቁ ማድረጉን የብሔረሰቡ ተወላጆች ተናገሩ።

የ"ጋሪ ዎሮ" በዓል "ጋሪ ዎሮ ለይቅርታ እና ለባህል ልማት" በሚል መሪ ሐሳብ በአሶሳ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።


 

በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የብሔረሰቡ ተወላጆች በዓሉ የአንድነት እና የወንድማማችነት እንዲሁም ሰላምን ለማስቀጠል ቃል የሚታደስበት ነው ብለዋል።

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ገረመው ደርሶ እንዳለው "ቦሮ ሽናሻ የእምቅ ባህልና እሴት ባለቤት ነው" ነው።


 

በዓሉ በተወላጆቹ ሲከበር መቆየቱን ገልጾ፤ ከአካባቢው አልፎ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች መከበሩ ደግሞ ሌሎች ማህበረሰቦች ስለብሔረሰቡ የሚያውቁበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብሏል።

ሌላዋ የብሔረሰቡ ተወላጅ ፅጌ ወንዳሳ በበኩሏ በዓሉ ሁሉም የብሔረሰቡ ተወላጆች በጋራ የሚያከብሩት ሲሆን፤ በተለይም ሴቶች ደግሞ በባህል ልብስ እና ጌጣጌጥ ደምቀው የሚታዩበት እንደሆነ ገልፃለች።


 

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካለች አልቦሮ እንዳሉት፤ የብሔረሰቡ ቱባ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ምሁራን እና የብሔረሰቡ ተወላጆች በጋራ መስራት አለባቸው።


 

አፈ ጉባኤዋ "ጋሪ ዎሮ" የይቅርታ በዓል በመሆኑ በብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል ጥላቻ እና መከፋፈል መኖር የለበትም ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዓሉ ነገ በአሶሳ ከተማ አዳባባይ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ይከበራል።

የቦሮ ሽናሻ የዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" መስከረም 12 ቀን 2017ዓ.ም በአዲስ አበባ በደማቅ ስነ-ስርዓት መከበሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም