ቀጥታ፡

በተለያዩ የሙያ መስኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ማዳበር ይገባል- አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፤መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፦በተለያዩ የሙያ መስኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት አስፈላጊ በመሆኑ የኮደርስ ሥልጠና ዕድልን መጠቀም እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ"5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ" ሥልጠና ኢኒሼቲቭን ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች በቴክኖሎጂ እውቀት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ነው።

በዚህም መሠረት በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኮደርስ ሥልጠና ወስደው የምስክር ወረቀት የሚያገኙ ይሆናል።

በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።

በዚህ ብሔራዊ የሥልጠና ፕሮጀክት መሠረትም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ዜጎች በመሰልጠን ላይ ሲሆኑ በአፋር ክልልም በተመሳሳይ ሁኔታ ተጀምሯል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ በክልሉ የኮደርስ ሥልጠና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕከል ባደረገ መልኩ ተጀምሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት አስፈላጊ በመሆኑ ዜጎች ዕድሉን እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

የ5 ሚሊየን የኮደርስ ሥልጠና ዕድል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማግኘት በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት በሥራ ስምሪት ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ዜጎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎትን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በአፋር ክልል ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ በተለያዩ መንገዶች የመረጃና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የክልሉ ወጣቶችና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥልጠና ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርኃ-ግብሩ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ዜጎች በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማሰልጠን ይሆናል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አካል የሆነው የኮደርስ ሥልጠና በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት ትብብር የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም