እንደ ደመራው በአንድነት ቆመን ሰላምን እናብራ - ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ - ኢዜአ አማርኛ
እንደ ደመራው በአንድነት ቆመን ሰላምን እናብራ - ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2017 ዓመተ ምህረት የመስቀል እና ደመራ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፣ አደረሰን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል!
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2017 ዓመተ ምህረት የመስቀል እና ደመራ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ! አደረሰን!
ለረጅም ጊዜ ተደብቆ እና ተሰውሮ የነበረው የጌታችን እና የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በሰማያዊ ብርሃን እና በአምላካዊ ምሪት የተገኘበትን የከበረ ታላቅ አመታዊ በዓል ለማክበር የክርስትና እምነት መሪዎች፣ አባቶቸ እና ተከታዮች በተዘጋጀንበት በዚህ ቀን፤ በዓሉን ስናከብር እንደ ደመራው በአንድነት ለመቆም እና ሰላምን ለአለም ለማብራት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡
የደመራው ብርሃን የአካባቢውን ጨለማ እንደሚገፈው ሁሉ እኛም እርስ በርሳችን ተደጋግፈን በመቆም እንደ ደመራው ብርሃን በአካባቢያችን ያለውን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የግጭት እና የጦርነት ጨለማ በማስወገድ፤ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ መደጋገፍን፣ በጎነትን እና ርህራሄን ለአለም ሕዝብ ሁሉ ከፍ አድርገን ማብራት ይጠበቅብናል፡፡
እነዚህንም መልካም ተግባራት መፈጸም እንችል ዘንድ እግዚአብሄር አቅም እንዲሰጠን በንጹህ ሕሊና ልባችንን ለፈጣሪ በመክፈት የእርሱን እርዳታ ልንጠይቅ እና እጆቻችንን ደግሞ በዙርያችን ያሉትን ሰዎች በሙሉ ያለልዩነት ለመደገፍ፣ አብረናቸው ለጋራ ጥቅም ለመኖር እና ለመሥራት መወሰን ይገባናል፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ አስደናቂ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች መገኛ ሃገር ናት፡፡ ከእነዚህ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ውስጥ እርስ በእርስ መዋደድ፣ መረዳዳት፣ መከባበር፣ በጎ ማሰብ እና ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ደግሞ እነዚህን ድንቅ የአብሮነት እና የሰላም መሰረት የሆኑትን እሴቶች ያለ ልዩነት ከቅዱሳት መጽሕፍት በመነሳት ለተከታዮቻቸው ያስተምራሉ፣ በተግባርም በሕይወታቸው እና በኑሮአቸው ይተገብሯቸው ዘንድ ያሳስባሉ፣ ያበረታታሉ እንዲሁም ይደግፋሉ፡፡
ነገር ግን እንዲ አይነት አስደናቂ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ያላት ሃገር በሰላም ማጣት፣ በግጭት፣ በጥላቻ መታወቋ፤ በተያያዘም ለመስማማት፣ ለመቀራረብ፣ ለፍቅር፣ ለመተጋገዝ እና ለአንድነት ምክንያት ከመፈለግ ይልቀ ለጠብ፣ ለጥላቻ፣ ለመለያየት፣ ለመራራቅ፣ ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን ከተለያዩ ምንጮች በመፈለግ ቅራኔ፣ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ በተደጋጋሚ መግባታችን ገፅታችንን ከማበላሸቱም ባለፈ የማደግ እና የመለወጣችንን ተስፋ እያደበዘዘው ይገኛል፡፡
ይህን አሉታዊ ገፅታችንን ለረጅም ጊዜ በዘለቁ እና ሃይማኖታዊ መሰረት ባላቸው እሴቶቻችን በመቀየር ከግጭት ይልቅ ለሰላም፣ ከመለያየት ይልቅ ለአንድነት፣ ከጥላቻ ይልቅ ለፍቅር፣ ከቂም እና ከበቀል ይልቅ ለይቅርታና ለመተው የሚረዱንን እውነተኛ ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን ከቅዱሳት መጽሕፍት በመውሰድ በአዲስ ልቦና አምላካችን የሚውደውን የብርሃን ሥራ በተግባር ለመሥራት ዛሬ በአንድነት እንድንነሳ በታላቁ እግዚአብሄር ስም ከልብ እጠይቃለሁ፡፡
በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መስቀል በዓልን ስናከብር መስቀሉ በአምላክ ብርሃን እና ምሪት ከተሰወረበት እና ከተደበቀበት እንደተገኘ ሁሉ ሃገራችን ኢትዮጵያ የጠፋባትን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተባበር በአምላካችን ብርሃን እና ምሪት ፈልገን ለማግኘት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል በመወን ሊሆን ይገባል፡፡
እኛ ለሰላም እና ለፍቅር ለመሥራት ከልብ ወስነን ከተነሳን እግዚአብሄር ብርሃኑን፣ ምሪቱን እና ኃይሉን ስለሚሰጠን ለተራራቁ መቀራረብን፣ ለተጣሉ ፍቅርን፣ ለተለያዩ አንድነትን፣ ለደከሙ ብርታትን፣ ለተቸገሩ መፍትሄን እና ሰላም ላጡ ሰላምን ማጎናጸፍ እንችላለን፡፡
አምላካችን እግዚአብሄር መለያየትን አጥብቆ ይጸየፋል፤ አንድነትን ደግሞ ይወዳል፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር ምዕራፍ 133 ቁጥር 1 ላይ “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፤ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” በማለት የሚናገረው፡፡
በመሆኑም እንደ ደመራው በአንድነት ተደምረን፤ እንደ ደመራው ብርሃን ደግሞ ሰላምን፣ እቅርን፣ አንድነትን፣ መረዳዳትን ከፍ አድርገን አብርተን ይህን የ2017 ዓመት ምህረት የብርሃነ መስቀል በአል በተሟላ ድምቀት እንድናከብር በድጋሜ በፈጣሪ ስም አደራ እላለሁ፡፡
በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2017 ዓመተ ምህረት የመስቀል እና ደመራ ክብረ በአል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፣ አደረሰን በማለት ልባዊ ምኞቴን በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በራሴ ስም በአክብሮት አቀርባለሁ፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይጠበቅ! አሜን!
All reactions:
2828
