በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 6 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር አረቦን መሰብሰብ ተችሏል - የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ - ኢዜአ አማርኛ
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 6 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር አረቦን መሰብሰብ ተችሏል - የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፦በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 6 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር አረቦን መሰብሰብ እንደቻለ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አስታወቀ።
ፈንዱ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 7 ነጥብ 3 ቢሊየን አርቦን በመሰብሰብ በተገቢው ኢንቨስትመንት ላይ ለማዋል ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም እና የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ ዝግጅትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር)፥ ፈንዱ ከአባል ፋይናንስ ተቋማት ዓርቦን መሰብሰብ፣ የተሰበሰበን ዓርቦን በመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እና አንድ የፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ ተቋሙን በመተካት ለገንዘብ አስቀማጮች ከ90 ቀናት ባነሰ ጊዜ መክፈል የሚሉ ሶስት ዋና ዋና ተግባራትን ያከናውናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጭ ሁሉም የግል ባንኮች እና ሁሉም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አባል መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፈንዱ እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ የመድን ሽፋን በመስጠት ከ100 ሺህ ብር በታች ተቀማጭ ገንዘብ ላለው ግለሰብና ድርጅት ፈንዱ ሙሉ በሙሉ ገንዘቡን ተመላሽ የሚያደርግለት መሆኑን ተናግረዋል።
ከብር 100 ሺህ በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ላለው ግለሰብ ወይም ድርጅት እስከ 100ሺህ ብር ያለውን ገንዘብ ፈንዱ ተመላሽ በማድረግ ቀሪውን ገንዘብ በወደቀው የፋይናንስ ተቋም ተጣርቶ ተመላሽ ሊደረግ እንደሚችል አስረድተዋል።
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመትም ተቋማዊ መዋቅርና አደረጃጀት፣ የአስፈላጊ መመሪያና የስራ ማስኬጃ በጀት ዝግጅት እንዲሁም ለቀጣይ ስራ አጋዥ የሆኑ የስራ መግባቢያ ስምምነት መደረጋቸውን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ዕቅድ መሰረት ከፈንዱ አባል የፋይናንስ ተቋማት ብር 6 ነጥብ 51 ቢሊየን አርቦን መሰብሰብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የተሰበሰበውን አርቦን በመጠቀም 6 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር ኢንቨስት ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 5 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር የሚሆነው ገንዘብ በመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ኢንቨስት የተደረገ ነው ብለዋል።
ቀሪው 539 ነጥብ 64 ሚሊየን ብር በሸሪዓ መርህ መሰረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሙዳራባህ ኢንቨስትመንት ሂሳብ መቀመጡን ገልጸዋል።
ፈንዱ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር አርቦን ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ፈንዱ በተጨማሪ የተሰበሰበውን አርቦን በአግባቡ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል የማስተዳደር አቅሙን ለማሳደግና ለጤናማ የፋይናንስ ተቋማት ተወዳዳሪነት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተጠሪነቱን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 482/2013 መቋቋሙ ይታወሳል፡፡
ፈንዱ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር እና ከኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ማኅበር በተወጣጡ አምስት የዳይሬክቶሬት ቦርድ ኃላፊዎች የሚመራ ተቋም ነው።