የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊከበር ይገባል-የአባ ገዳዎች ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊከበር ይገባል-የአባ ገዳዎች ሕብረት

አዲስ አበባ፤መስከረም 16/2017(ኢዜአ)፦የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊከበር እንደሚገባ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሕብረት ገለፀ።
የአባ ገዳዎች ሕብረት መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሆራ ፊንፊኔ እና በቢሾፍቱ የሆራ አርሰዴ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አከባበር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ እና የመጫ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ እንዳሉት፤የኢሬቻን በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል።
አሁን ላይ የኢሬቻ በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ሃብት በመሆኑ በዓሉ በተሳካ መልኩ ሊከበር ይገባል ብለዋል።
የኢሬቻ በዓል ከያዘው እሴት ውጭ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት ማንፀባረቂያ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ በዓሉን በተገቢው መልኩ እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፈዋል።
በዓሉ የእርቅ ፣የሰላምና የአንድነት በዓል መሆኑን ተከትሎ መላው ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ሊከበር ይገባል ብለዋል።
በዓሉን ሁሉም ያለምንም የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የእድሜ ልዩነት በጋራ የሚያከብሩት መሆኑንም ጠቁመዋል።