ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር ያሉባትን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ኮትዲቭዋር ላይ ታደርጋለች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ የሚያደርጋቸውን የምድቡን ሶስተኛና አራተኛ የማጣሪያው ጨዋታዎች በኮትዲቭዋር እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያውን ሦስተኛ ጨዋታ ጨዋታውን ጊኒ የሜዳዋ ጨዋታዋን ለማድረግ ባስመዘገበችው በኮትዲቯር ያሞሱክሩ የሚገኘው ስታድ ኮናን ባኒ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

አራተኛ የምድብ ጨዋታውን በተመሳሳይ ከጊኒ ጋር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሜዳውን ጨዋታ ለማድረግ ባስመዘገበው አቢጃን የሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ እንደሚያከናውን አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በሞሮኮ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ 8 ከታንዛንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ጊኒ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ብሔራዊ ቡድኑ እስከ አሁን ባደረጋችው ጨዋታዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ሲሸነፍ፣ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቱ የሚታወስ ነው።

ውጤቶቹንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስድስት ነጥብ ምድቡን እየመራ ይገኛል። ታንዛንያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች።

48 አገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።  

በአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም