በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16 /2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ፋሲል ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወቃል።
በዳንኤል ፀሐዬ የሚሰለጥነው መቀሌ 70 እንደርታ በመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር በሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 ተሸንፏል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያከናውናል።
ቡናማዎቹ በመጀመሪያ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ማድረግ ሊያደርጉት የነበረው መርሃ ግብር ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በነበረበት ጨዋታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።
በአንጻሩ በዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 3 ለ 2 መሸነፉ ይታወቃል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለሱ አይዘነጋም።
በተያያዘም ትናንት በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልቂጤ ከተማን በፎርፌ አሸንፏል።
ኢትዮጵያ መድንና አርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።