የጎፋና ኦይዳ ብሄረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የጎፋና ኦይዳ ብሄረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ
ሳውላ፤ መስከረም 15/2017 (ኢዜአ)፦የጎፋ “ጋዜ መስቃላ” እና የኦይዳ “የአ ማስቃላ” የዘመን መለወጫ በዓል በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳና በሳውላ ከተማ በተካሄደ የመስህብ ስፍራ ጉብኝትና የባህል ሲምፖዚየም ተከበረ።
በበዓሉ ላይ የጎፍኛ እና የኦይዳ ስነ-ቃልና ተረትን የያዘና በጎፍኛ፣ በኦይዳ እና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፉ ሶስት መጽሀፍት ለምረቃ በቅተዋል።
በዚሁ ጊዜ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ እንዳሉት የጎፋና የኦይዳ ህዝቦች በጋራ ተጋግዘውና ተረዳድተው ሚኖሩ በመሆናቸው ይህን አብሮ የመኖርና የመረዳዳት እሴት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል።
በጎፋ ዞን የሚገኙ ብሄረሰቦች ያላቸውን እሴት የሚያንጸባርቁባቸው የዘመን መለወጫ በዓል እንዲሁም ተረትና ምሳሌዎችን በጽሁፍ ለማስቀረት ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ወቅትም ተረቶች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና እንቆቅልሾችን በማሰባሰብ በመጽሀፍ መልክ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያግዙ ሶስት መጽሀፍት በጎፋ፣ በኦይዳና አማርኛ ቋንቋዎች መታተማቸውን ገልጸዋል።
መጽሀፎቹ የቋንቋ ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲዎች በማሰባሰብ የብሄረሰቦቹን ቱባ ባህል ሳይለቅ እንዲጻፉ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ታሪኩ ኦቻ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦች መገለጫ የሆኑ እሴቶችን በመጽሀፍ መልክ በማሳተም ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በጎፋ ዞን የሚገኙ ብሄረሰቦችን ስነ-ቃልና እንቆቅልሾች በማሰባሰብ በሶስት ቋንቋዎች እንዲታተሙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፋይናንስ ቢሮ ላደረጉት ትብብርና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የዘመን መለወጫ በዓሉ በኦይዳ ወረዳ 'ሰአጉላ' ወይም የመሬት እምብርት ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ በእግር ጉዞ፣ በሲምፖሲየዘም፣ የባህላዊ አልባሳት ፋሽን ትርኢትና በደመራ ማብራት ስነ-ስርዓት ተከብሯል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና ሌሎች አመራሮችን ጨምሮ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎችና የተለያዩ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።