የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በቀጣዩ ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በቀጣዩ ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በቀጣዩ ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ፤ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ከጥቅምት 2 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
የውድድር መድረኩ በግንቦት ወር ኳታር ላይ ለሚደረገው የዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች የሚመረጡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሀገራቱ ለዚህ ውድድር ተሳታፊነት የበቁት፤በአምስት ምድብ ተከፍለው የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ማጣሪያ ውድድር ከተደረገ በኋላ የየምድቡ አሸናፊዎች በመሆን ነው።
በአራት ዓይነት ዘርፎች በቡድን፣በነጠላ፣በጥንድና በድብልቅ በሁለቱም ፆታዎች የሚከናወን ውድድር ሲሆን ለአሸናፊዎች የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ውድድሩ መካሄዱ የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርትን ለማነቃቃት አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ከፍተኛ የበጀትና የቁሳቁስ እጥረት ያለበት በመሆኑ ውድድሩ በመዲናዋ መዘጋጀቱ ከዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ለማግኘት አስችሏል ብለዋል።
በድጋፉም የጠረጴዛ ቴኒስ ምንጣፍ፣የማጫወቻ ጠረጴዛና ኳስ፣ ራኬትና መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እንደተበረከተ ገልፀዋል።
ከውድድሩም መጠናቀቅ በኋላ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
በጉባዔውም የፌዴፌሬሽኑ አባል ሀገራት ፕሬዝዳንቶችና ተወካዮች በተገኙበት እንደሚከናወንም ነው የገለፁት።
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አባል የሆነው በ1964 ዓ.ም ሲሆን፤ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናን ሲያዘጋጅ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።