ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ሥጋት እንዲከበር በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ያለምንም የጸጥታ ሥጋት በሰላም እንዲከበር በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመተባበር የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ለማክበር የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ቱሪስቶች የሚታደሙበት ስለመሆኑ አንስተዋል።


 

የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ በመስቀል አደበባይ በዓሉ ሲከበር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሃብትና የዓለም ቅርስ የሆነው በዓል በመላ ኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ ይዘቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ሥጋት በሰላም እንዲከበር በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የዳበረ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ለበዓሉ ፍጹም ሰላማዊነት ሁሉንም የቴክኖሎጂ አቅሞች እንጠቀማለን ብለዋል፡፡


 

ፖሊስ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የጸጥታ ካሜራዎች፤ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው መረጃ የሚያመጡ ድሮኖች እንዲሁም ድርጊቱን በቀጥታ የሚከታተሉበት ማዕከል እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በጀግንነት የሚጠብቁ በሰብዓዊነት የሚያገለግሉ የጸጥታ አባላት አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ስምሪት ወስደው ሥራ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ ክልከላዎች በማክበር የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው፤ የመስቀል ደመራ በሚደመርበት ወቅት ርችት መተኮስ የተከለከለ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ጸረ ሰላም ሀይሎች በርችት ሰበብ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጥሩ ህብረተሰቡ ርችት ከመግዛትም ሆነ ከመሸጥ መታቀብ አለበት ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ፤ በዓሉን በሰላም ለማክበር ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የቅድመ መከላከል ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በመዲናዋ የተደራጁ ወንጀሎችን፤ የሽብር ሙከራዎችን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በሚገባ መመከት ተችሏል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ፖሊስ ከህብረሰተቡ ጋር በመተባበር በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ መዲናዋን ከወንጀል ሥጋት ነፃ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ፤ በመዲናዋ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የሚያረጋግጡ የህግ ማስከበር ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡


 

በአዲስ አበባ ፖሊስ የኮልፌ ቀራኒዮ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ግርማ ተሰማ፤ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡


 

የመስቀልና ደመራ በዓል ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ተጠናቋል ሲሉ ተናግረዋል።




በአዲስ አበባ ፖሊስ የየካ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዓለማየሁ አያልቄ፤በመስቀል አደባባይም ሆነ በየአድባራቱ የሚከበሩ በዓላት ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ከሀይማኖት አባቶችና ከማህበረሱ ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም