ቀጥታ፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ስልቶችን የሚያስተገብሩ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ ምዕራፎችን እያለፈ ነው 

አዲስ አበባ፤መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ ምዕራፎችን እያለፈ መሆኑን የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ መድረክ አመራር ሴክሬታሪያት ኃላፊ አዎል ሱልጣን ገለጹ።

ፖሊሲው በእውነት ማፈላለግ፣ በወንጀል ተጠያቂነት፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ በተመሠረተ ምህረት፣ በማካካሻና ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረግ ሰብዓዊ መብትን ማስከበር መነሻና መዳረሻውን ያደረገ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 09 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማጽደቁ ይታወሳል።

የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ መድረክ አመራር ሴክሬታሪያት ኃላፊ አዎል ሱልጣን፤ ብቃት ባላቸው ገለልተኛ የሕግ ባለሙያዎች አማካኝነት አሳታፊና አካታች በሆነ መድረክ የሀገርን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የተሻለ ለማድረግ ፖሊሲው መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና በክልል ከተሞች በተካሄዱ ከ80 በላይ መድረኮች ከ4 ሺህ በላይ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

13 የባለሙያ ቡድን አባላት በመድረኮች የተሰጡ ግብዓቶችን በማሰባሰብና የመጨረሻ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና የፕሪቶሪያ ስምምነት ምክረ-ሃሳቦችም የተፈጠሩ ሀገራዊ ስብራቶችን ለማከም ለፖሊሲው ዝግጅት ምክንያት ከሆኑት መካከል እንደሚካተቱ ጠቅሰዋል። 

የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት መዳኘት አዳጋች በመሆኑ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። 

በዚህ መነሻነት የተፈጠሩ ችግሮችን በመለየት ስብራቶችን መጠገን የሚያስችል ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እርቅን ማውረድና ማካካሻ መስጠት ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ መገንባት የፖሊሲው ወሳኝ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል። 

የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በእውነት ማፈላለግ፣ በወንጀል ተጠያቂነት፣ በቅድመ-ሁኔታ በተመሠረተ ምህረት፣ በማካካሻና ተቋማዊ ማሻሻያ መፍትሔ መስጠት የፖሊሲው መሠረት ናቸው ብለዋል። 

የሽግግር ፍትሕና የሀገራዊ የምክክር ሂደቶች መዳረሻ ዓላማቸው ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር የሚያስችል መደላድል መዘርጋት መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ከሚመለከታቸው ተቋማትና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ተግባር ለመለወጥ የማስተባበር ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። 

የፖሊሲውን የማስፈጸሚያ ስልቶች ተግባራዊ ማድረግ፣ ተቋማትን መገንባትና ማቋቋም የሚያስችሉ ምዕራፎችን በሂደት እያለፈ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በተሻለ መልኩ ለመወሰን በተዘጋጀለት ፍኖተ-ካርታ መሠረት በጥንቃቄ እየተመራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በፍኖተ-ካርታው መነሻነት የሚቋቋሙ ተቋማት የሚመሩበት የልዩ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ፣ የእውነት (ሀቅ) አፈላላጊ፣ የተቋማት ማሻሻያ፣ የልዩ ችሎትና የዓለም አቀፍ ወንጀል ጉዳዮችን ለመደንገግ የሚወጡ አምስት የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በቀጣይም በአምስቱ ሕግ ማዕቀፎች ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ ከ25 በላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ በማካሄድ ሰነዶቹን ለማጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለዚህም በፖሊሲ የተመላከቱ የፖሊሲ አቅጣጫ ስልቶችን ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ በማጠናቀቅ የማረምና ለግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የማዘጋጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።  

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ሳይዘገይም በጣም ሳይቻኮልም በልዩ ጥንቃቄ ተግባር ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም