የፓኪስታን ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በአልሙኒየም፣ ብረታ ብረትና የፓኬጂንግ ወረቀት ምርት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
በኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ሰለሞን የፓኪስታን ባለሃብቶችን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ በውይይቱ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ያሉ መሠረተ ልማቶችን፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እና ጠቀሜታዎች ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
አቶ ሽፈራው በአገሪቱ ያለው ወጣትና የተማረ የሰው ሃይል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲሁም በመንግስት በኩል የተሠጠው ከፍተኛ ትኩረት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ኢንቨስት ለማድረግ ትክክለኛ ቦታ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የፓኪስታን ባለሃብቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኩል ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታና አማራጮች መኖራቸውን ገልጸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በአልሙኒየም፣ ብረታ ብረትና የወረቀት ፓኬጂንግ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችላቸውን የቅድመ ኢንቨስመንት ጉብኝት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነጻ የንግድ ቀጠና የፓኪስታን ባለሃብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡