ቀጥታ፡

የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም 43 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ አድርጓል - የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017 (ኢዜአ)፦ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት የመስኖ አውታሮችን በመገንባትና የውሃ አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት 43 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የልማት ፕሮግራሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።

በግብርና ሚኒስቴር ሲተገበር የቆየው ፕሮግራም የምግብ ዋስትና ክፍተት ባለባቸው አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት በመድረስ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ አላማ ያለው ነው።

የምዕራፍ ሁለት መርሃ ግብር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ሲተገበር ቆይቷል።

በፕሮግራሙ አማካኝነት ለአርሶ አደሮች የመስኖ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት በተለያዩ በግብርና ልማትና ተጓዳኝ ስራዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ በአነስተኛ መስኖ ልማት ላይ በተከናወነው ስራ በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አመልክተዋል።

ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም አርሶ አደሮች ቀጣይነት ያለው ገቢ እንዲኖራቸው፣ የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጡና አደጋን የመቋቋም አቅም እንዲፈጥሩ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

ፕሮግራሙ 112 አነስተኛ መስኖ አውታሮችን በመገንባትና 1 ሺህ 651 የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመፍጠር 43 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በፕሮግራሙ 183 ሺህ 23 ሄክታር መሬት እንደለማም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ጨምሮ የልማት ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት ብሔራዊ አስተባባሪ ኑረዲን አሳሮ በበኩላቸው በፕሮግራሙ የተተገበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማዊራ ቺቲማ በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋሙ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል ባደረገፍ ድጋፍ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢፋድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር መስራቱንና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሪፖርት ቀርቦ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን ፕሮግራሙ ሲተገበርባቸው በቆዩ ክልሎች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ቀርበዋል።

ክልሎቹ በፕሮግራሙ ያከናወኗቸውን ስራዎች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ተካሄዷል።

በፕሮግራሙ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የእውቅና እና የሽልማት ስነ ስርዓት መካሄዱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም