ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ከ32 ሺህ በላይ የድሬዳዋ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ

ድሬዳዋ ፤መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ከ32 ሺህ በላይ የድሬዳዋ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ እና ክህሎት ቢሮ እና የአስተዳደሩ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮጀክትን በድሬዳዋ ለመተግበር እየተከናወኑ የሚገኙትን ዝግጅቶች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የአስተዳደሩ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፈጡም መስጠፋ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት በአስተዳደሩ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን በስፋት እና በጥራት ዕውን ለማድረግ የተቀናጀ ስራ ይሰራል።

የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ኮደርስ የቴክኖሎጂ ስልጠና ፕሮጀክት በዚህ ወር ወደ ተግባር ለማሸጋገር የቅደመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ የሚሰለጥኑ ወጣቶች ዓለምአቀፍ የምስክር ወረቀት የሚያገኙ እና በዘመኑ የዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪና ተመራጭ የስራ ፈጣሪ ለመሆን እንደሚችሉ በማከል።

የኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ለሶስት ዓመታት የሚዘልቅ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በአስተዳደሩ ከ32 ሺህ በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በአስተዳደሩ በዚህ ወር በሚጀምረው የኮዲንግ ስልጠና ስምንት ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም በማውሳት።

 

የአስተዳደሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ኢንጂነር አብዱልአዚዝ ሻፊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ፕሮጀክት  በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን  ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ለመሳካት እና ለአገር ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ ከፍተኛ አበርክቶ አለው ብለዋል።

በተለይም ወጣቶች በዘመነ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና ስራ ፈጣሪ ሆነው ለአገር ዕድገት ሚናቸውን እንዲወጡም መሠረታዊ ክህሎት ያስጨብጣል ብለዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የድሬዳዋን 180 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዲጂታላይዝ  ለማድረግ እና ድሬዳዋ ስማርት ሲቲ እንድትሆን ለተጀመረው ጥረት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ለስልጠናው 400 ኮምፒውተሮችና 20 የመማሪያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ፣ ሁለቱ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች እና ሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለፕሮጀክቱ መሳካት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም