የአደባባይ በዓላት የእምነት፣ የባህልና ታሪካዊ ትውፊቶች ማሳያና የሀገር ውብ ገጽታ ምልክቶች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአደባባይ በዓላት የእምነት፣ የባህልና ታሪካዊ ትውፊቶች ማሳያና የሀገር ውብ ገጽታ ምልክቶች ናቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላት የእምነት፣ የባህልና ታሪካዊ ትውፊቶች ማሳያና የሀገር ውብ ገጽታ ምልክቶች መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኝዎች ታድመውባቸውና ምዕመናን ተሳትፈውባቸው በየዓመቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት አሉ።
ከክብረ-በዓላቱ መካከል ከሀገር ኃብትነት በመሻገር የዓለም ቅርስ በመሆን የሚጠቀሱም አሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን የኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላት የእምነት፣ የባህልና ታሪካዊ ትውፊቶች ማሳያና የሀገር ውብ ገጽታ ምልክቶች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተርና የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር ግርማ በላቸው(ዶ/ር)፤ የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያ ለዓለም የምትታይባቸው መድረኮች፣ የሀገር ውበት መገለጫ፣ የአብሮነት፣ የባህል እና የታሪክ ማሳያዎች መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም እነዚህን ሀገራዊ ኃብቶችና ቅርሶች የአከባበር ትውፊታቸው ሳይሸራረፍ በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ተመራማሪው መምህር መክብብ ገብረማሪያም፤ የአደባባይ በዓላት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየአካባቢው ያለውን ጸጋ ጭምር የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መገለጫ የሆኑ የጋራ የሀገር ኃብቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መካከል የፊታችን ሐሙስና ዓርብ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል እሴቱና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲከበር ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት እንዲሆን ባለሙያዎቹ አስገንዝበዋል።