ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጣልያን ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ 20 ለማድረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጣልያን ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ ከ14 ወደ 20 ለማድረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጣልያን ሮም በረራ የጀመረበትን 60ኛ ዓመት አስመልክቶ በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ አክብሯል።


 

በመርኃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓልሴ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ፣ አምባሳደሮችና ሌሎችም የአየር መንገዱ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ ላለፉት 60 ዓመታት ወደ ጣልያን ሮም ያደረገው በረራ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን ገልፀዋል።

የበረራው አገልግሎቱ ከምጣኔ ኃብት ትስስርም ባለፈ የጣልያንና የአፍሪካ አገራትን ግንኙነት ያሳደገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዛሬ 60 ዓመት ወደ ሮም በሳምንት ሁለት ጊዜ መብረር መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ ሮምና ሚላን በሳምንት 14 ጊዜ እየበረረ አገልግሎቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱ ከሦስት ወራት በኋላ ወደ ጣልያን ከተሞች የሚያደርገውን በረራ በሳምንት 20 ለማድረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓልሴ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ከማገናኘትም ባለፈ የላቀ አህጉራዊ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

አፍሪካን ከአውሮፓና ሌሎች አህጉሮች ጋር በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት የምጣኔ ኃብት ትስስሩ እንዲጎለብት በማድረግ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይም በጣልያንና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት፣ ማኅበራዊና የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማጠናከር ባለውለታ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱ ወደ ጣልያን ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ ለማሳደግ መዘጋጀቱ ለሁለቱ አገራት ሌላ ተጨማሪ ጥቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በ147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም