ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ።

ኢትዮጵያ መድን ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በመጀመሪያው ሳምንት አራፊ ቡድን የነበረው ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደርጋል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ አምና በሊጉ በ40 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በበረከት ደሙ የሚሰለጥነው አርባምንጭ ከተማ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 1 መሸነፉ ይታወቃል።
አርባምንጭ ከተማ ባለፈው ዓመት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም መመለሱ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርሃ ግብር ወጥቶላቸዋል። 

ወልቂጤ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር አስገዳጅ የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ ባለማግኘቱ ምክንያት በመቻል በፎርፌ መሸነፉ ይታወቃል።

ክለቡ እስከ አሁን የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ አለማግኘቱን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ወልቂጤ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላ የክለብ ላይሰንሲንግ ፈቃድ እንደሚያገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ወልቂጤ ከተማ የክለብ ላይሰንስ ፈቃድ ማግኘቱን የሚያሳይ መረጃ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንዳልተላከለት አመልክቷል።

ቡድኑ ፈቃዱን አሟልቶ ጨዋታውን ማድረግ ካልቻለ የፎርፌ ውጤት ለተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚሰጥ ገልጿል።

በሊጉ የዲሲፕሊን መመሪያ አንድ ቡድን በውድድር ዓመቱ ሁለት ጊዜ በፎርፌ ውጤት ከተሸነፈ ከሊጉ እንደሚታገድ ማህበሩ ገልጿል።
ወልቂጤ ከተማ በዛሬው ጨዋታ በፎርፌ ከተሸነፈ ከውድድሩ ይታገዳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በነበረበት የመልስ ጨዋታ ምክንያት በመጀመሪያ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።

ንግድ ባንክ የዋንጫ ክብሩን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጉዞ ወልቂጤ ከተማን በመግጠም ይጀምራል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ቡድን በ2016 የውድድር ዓመት በ64 ነጥብ የሊጉ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ፋሲል ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 10 ሰዓት፣ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና የሁለተኛ ሳምንት አራፊ ቡድን ነው።

የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያሉ።

በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19 ክለቦች እየተወዳደሩ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም