የኢትዮጵያ ውኃን ማዕከል ያደረገ የኃይል ልማት ከብክለት ነፃ ለሆነ ልማት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ውኃን ማዕከል ያደረገ የኃይል ልማት ከብክለት ነፃ ለሆነ ልማት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ውኃን ማዕከል ያደረገ የኃይል ልማት ከብክለት ነፃ ለሆነ ልማት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ኃብት ዘርፍ ተመራማሪና መምህር ኤርሚያስ ተፈሪ(ዶ/ር) ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተስተካከለ የውኃ ፍሰት የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት በመቀነስ እንዲሁም የአካባቢውን ሀገራት የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በዘርፈ-ብዙ ፋይዳነቱ የሚነሳ ነው።
የግድቡ መገንባት የደረቅ ወቅት የውኃ ፍሰትን በ25 ከመቶ በማሳደግ ባልተቋረጠ የውኃ ፍሰትና በትነት የሚጠፋን የውኃ መጠን 12 ከመቶ በማመጣጠን ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጉልህ አስተዋጽዖ የሚኖረው ይሆናል።
የኢትዮጵያ ውኃን ማዕከል ያደረገ የኃይል ልማትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ኃብት ዘርፍ ተመራማሪና መምህር ኤርሚያስ ተፈሪ (ዶ/ር)፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባትና ዘላቂ የምጣኔ ኃብት ተጠቃሚነት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሀገርም ባለፈ ቀጣናዊ ተጠቃሚነትን እውን በማድረግ የላቀ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ከግድቡ የሚመነጨው 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ከብክለት ነፃ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል የቀጣናውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግና የኃይል አቅርቦት ትስስር እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውኃን ማዕከል ያደረገ የኃይል ልማት ከብክለት ነፃ ለሆነ ልማት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ ዶክተር ኤርሚያስ አብራርተዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የመስኖ ልማት ለደለልና የጎርፍ አደጋ እንዳይጋለጥ የግድቡ መገንባት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለመደበኛ የሰብል ልማትም ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የይቻላል መንፈስ በተግባር ያሳየ ብሔራዊ ኩራትና የስኬታማነት ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
ግድቡ 1 ሺህ 280 ኪሎ ሜትር ስኩዬር ስፋት ያለው ግዙፍ የውኃ አካል መፍጠር ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ ለግድቡ እውን መሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያደረጉት የላቀ አስተዋጽዖ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረግ ጫና ተቀባይነት የሌለውና የልማት ፍላጎትን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ብሔራዊ የተደራዳሪ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላትም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሲደረግ የነበረን ጫና ለመቋቋም ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
"አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካውያን መፍታት" በሚል መርህ የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን መፈረማቸው የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስጠብቅ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቅርቡ ደቡብ ሱዳን የናይል ትብብር ማዕቀፉ ላይ ፊርማዋን ማሳረፏም የናይል ቤዚን ኮሚሽንን ማቋቋም የሚያስችል ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ገልፀዋል።
የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ከተሜነትና የኢንዱስትሪ ልማት የኃይል ፍላጎት በማሟላት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና የመልማት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።