ቀጥታ፡

በሮቤ ከተማ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው

ሮቤ፤ መስከረም 15/2017 (ኢዜአ)--በሮቤ ከተማ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን ኑሮ በማሻሻል በኩል ጉልህ አስተዋጾ እያበረከቱ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ። 

በከተማዋ የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ሥራዎችን በማስመልከት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ የመሰረተ ልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪውን ኑሮ በማሻሻል በኩል ጉልህ አስተዋጾ እያበረከቱ ነው። 

በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማትም አስፈላጊ፣ ወቅቱን የዋጀ እና ለሌሎች ከተሞች በምሳሌነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የነዋሪዎችን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና የሮቤ ከተማን የንግድና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል በተመረጡ የከተማዋ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ አንዱ ነው። 


 

በልማቱ ላይ አስተያየት ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ በከር አህመድ እንዳሉት፣ በተለይ በከተማዋ የተከናወኑ የመንገድ ዳር ልማቶች የተሽከርካሪና የእግረኞች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆኑ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። 

በከተማዋ የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተለይ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር ታሳቢ ተደርገው እንደተገነቡ ማየታቸውን የገለጹት ደግሞ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው።  

አስተዳደሩ እያከናወነ ያለው ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሥራ የከተማዋን ነዋሪዎች ያማከለና ተጠቃሚ  ያደረገን በመሆኑ ለልማቱ የበኩላችንን አስተዋጾ ለማበርከት ዝግጁ ነን ሲሉም ገልጸዋል። 

በጥቃቅን የንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት አቤል መንግሥቱ በበኩሉ እንዳለው፣ በከተማዋ ከዚህ በፊት የጽዳት ችግሮች እንደነበሩ አስታውሷል። 

በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ውብና ጽዱ ከማድረግ ባለፈ እሱን ጨምሮ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናገሯል።


 

አቶ ኢሳ ጣሂር የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ ከተማዋ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ለሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች መዳረሻ ሆና እያገለገለች መሆኗን ገልጸዋል። 

በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ሥራዎች የነዋሪውን ህይወት ከማሻሻል ባለፈ የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ በኩል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። 

በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የውስጥ ለውጥ የአስፋልት መንገዶች በተለይ የከተማዋን ውበት በመጨመር ለነዋሪው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር መሳለጥ የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፎዚያ ጣሓ ናቸው። 


 

"በከተማዋ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የድርሻዬን ለመወጣት እጥራለሁ" ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች በምሳሌነት የሚወሰዱና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆኑ በሚችሉት ሁሉ ልማቱን እንደሚደግፉ ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። 

በሮቤ ከተማ አስተዳደር የ15 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውጥ የአስፋልት መንገድ፣ የመንገድ ዳር የቴራዞ ንጣፍ ሥራ፣ የንግድ ሼዶች፣ የአረንጓዴ እና ሌሎች የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

እነዚህ የልማት ሥራዎች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እየተከናወኑ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም