ቀጥታ፡

በክልሉ የደመራና የመስቀል በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ):- የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የደመራ እና መስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን እንደገለጹት የደመራ እና የመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር የክልሉ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ፣ ከፌደራል ፖሊስና ከሚሊሻ ኃይል ጋራ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታ እቅድ ወጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው ለሁሉም ፈፃሚና አባላት እንዲሁም አጋዥ ተቋማት የበአሉን አከባበር በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የማድረግና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ከኮሙዩኒቲ ፖሊሲንግ አደረጃጀቶች እና ከሰላም አምባሳደሮች እና ከክልሉ ህብረተሰብ ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን ከማድረግ አንፃርም የትራፊክ ክፍሉ አስፈላጊውን ዝግጅት ማደረጉን ተናግረዋል።

በከተማው የደመራ ስነ-ስርዓት ወደ ሚከናወንበት ስፍራ ከበዓሉ አከባበር ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ነገሮች ይዞ መምጣት ክልክል መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ለፀጥታ ሃይሎች ሥራ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ሕብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም በዓሉ በሰላም እንዲከበር የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

ነዋሪዎች በበዓሉ አከባበር ወቅት አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አልያም በኮሚሽኑ 8842 የነፃ ጥሪ ማዕከል ጥቆማ እንዲሰጡም ነው ያመለከቱት።

በዓላቱ የሰላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም