የተራቆተ ተራራን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ የለወጡት ብርቱዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተራቆተ ተራራን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ የለወጡት ብርቱዎች
ሀጂ ተማም መሐመድ እና የማህበሩ አባላት ከጥቂት ዓመታት በፊት ምንም ነገር እንዳልነበራቸው ይናገራሉ።
በሃጂ ተማም መሐመድ የሚመራውና ስድስት አባላት ያሉት ማህበር በአዳማ ከተማ ጫፍ ላይ የሚገኝና 'ጋራ ጮቆኑ' የሚባል የተራቆተ ተራራን በማልማት ነው ወደ ሥራ የገባው።
ሃጂ ተማም እንደሚሉት 'ጋራ ጮቆኑ' ተራራ በወቅቱ እሾሀማ፣ አሸዋማ እና ምድረ በዳ ሲሆን ከተራራነቱ በስተቀር ምንም ልምላሜ አይታይበትም ነበር።
በተራራው ላይ ማህበራቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ለምግብነት የሚውሉ አትልክትና ፍራፍሬዎችን በማልማቱ አካባቢው ልምላሜ ከመጎናጸፉ ባሻገር የማህበሩ አባላት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ማህበሩ ከአትክልትና ፍራፍሬ ባሻገር በተራራው ግርጌ የወተት ላሞችን በማርባት ከወተት ምርት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ሲሆን፤ የንብ ማነብ ስራንም ጎን ለጎን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተራራው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ማዕከልነት በመቀየሩ የማህበሩን አባላት ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ በትጋት ከተሰራ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ብዙዎችን ያስተማረ መሆኑንም ሃጂ ተማም አንስተዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ በአሁኑ ወቅት የማህበሩ አባላት በተራራው ላይ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ማንጎ እና ሽንኩርት እያመረቱ ይገኛሉ።
ምርቱንም ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የማህበሩ አባላት ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን በተሻለ ትምህርት ቤት እያስተማሩ ሲሆን፤ የተሻለ መኖሪያ ቤትም መገንባታቸውን ነው የገለጹት።
ሃጂ ተማም ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢያቸውን ወደ ልማት በመለወጥ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ መክረዋል።
በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ከድር አደም፣ በወረዳው የሚገኘውን 'ጋራ ጮቆኑ' ተራራ አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ በርካቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ይናገራሉ።
ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበር ተደራጅተው የተራቆተውን ተራራ አልምተው እንዲጠቀሙ እድል መስጠቱን ጠቅሰዋል።
በተለይም ሃጂ ተማም የሚመሩት ማህበር ተራራውን አረንጓዴ ማልበስ ከጀመረ ሦስት ዓመት እንደሆነውና እጅግ ውጤታማ መሆኑን ነው የገለጹት።
የማህበሩ አባላት በተራራው ላይ ችግኞችን ከመትከል በዘለለ ተከታታይነት ባለው እንክብካቤ አጥጋቢ ምርት እንዲሰጡ ማድረጋቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ከማህበሩ ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች የወረዳው ነዋሪዎችም ከጥላነት ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ ዛፎችን ተክለው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም እያንዳንዱ ቤት እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክሉ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማው ጎሮ ወረዳ ባሉ 84 ብሎኮች 68 ሺህ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች በክረምት ወቅት መተከላቸውን ተናግረዋል።