የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የቻይና ኤሌክትሮኒክስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የትብብር አድማሳቸውን ለማስፋት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የቻይና ኤሌክትሮኒክስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የትብብር አድማሳቸውን ለማስፋት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017 (ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የቻይና ኤሌክትሮኒክስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (UESTC) የትብብራቸውን አድማስ ለማስፋት በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ሁለቱ ተቋማት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙም ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የቴክኖሎጂ አማካሪ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) ከቻይና ኤሌክትሮኒክስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጓንግቹን ሉኦ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በማመቻቸትና በጋራ በመስራት በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የቴክኖሎጂ አማካሪ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ ዘርፍ ባመቻቸው ነጻ የትምህርት እድል ፕሮግራም (ስኮላርሺፕ) በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ የሚሰጠውን የትምህርት እድል እንዲያሰፋ ጠይቀዋል።
የቻይና ኤሌክትሮኒክስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (UESTC) የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጓንግቹን ሉኦ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሚኒስቴሩና ለተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች የትምህርት እድሎችን እንደሚያመቻችም ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በክህሎት ልማት ለቡራዩ የልዩ ተሰጥዖ ትምህርት ቤት ስልጠና እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።