አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2017(ኢዜአ)፦ በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር የጋራ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን በመግለጽ በቀጣይ የጋራ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ቀጣይነት ያለው ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር ታዬ ለረዳት ሚኒስትሯ በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በተለይ ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት ትኩረት ሰጥተው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ሶማሊያን በተመለከተ ከሞሊ ፊ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን በመዋጋት ረገድ በምታደርገው የተጠናከረ ጥረት ዙሪያ ገለጻ በማድረግ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ሥምሪት ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የስምሪቱ ማዕቀፍ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ በበኩላቸው አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና አጠቃላይ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።