ኤጀንሲው ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ  ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን  የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ ።

የኤጀንሲው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2030 ዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይልን  በሦስት እጥፍ በማሳደግ የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ የአየር ንብረት ለዉጥ ግቡን ማሳካት እንደሚቻል  አመልክቷል።

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በኒውዮርክ  የአየር ንብረት ሳምንት ላይ ለታደሙ ከመንግሥት እና ከንግዱ ዘረፍ  ለተውጣጡ ኃላፊዎች ሪፖርት ማቅረቡን ዘግቧል።

በዱባይ አምና በተካሄደው COP 28 የአየር ንብረት ጉባኤ 200 የሚጠጉ ሀገራት እንደ የንፋስና ፀሀይ ያሉ የታዳሽ ኃይሎችን በሦስት እጥፍ በማሳደግ በ2050  ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን ዘገባው አስታውሷል።

አገራት በ2030 ስምምነቱን  ሙሉ በሙሉ በመተግበር ጥቅም ላይ ለማዋል 25 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመገንባት እና ለማዘመን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም  አንስቷል።

በዚህም  በ2030 ዓለም 1 ሺህ 500 ጊጋዋት የኃይል ማከማቻ አቅም እንደሚያስፈልጋት ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

አገራት በCOP 28 የኃይል አጠቃቀምን የሚረዱትን የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ለማሳደግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ዉጤታማነቱ መንግሥታት  ለፖሊሲዎቻቸዉ ቅድሚያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን አመላክቷል።

በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት መሰረት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሀገራት ታዳሽና የኢነርጂ ውጤታማነት ግቦችን በአገራዊ ዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት አለባቸው ሲል ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማሳሰቡን ዘገባው ያመለክታል።

ከዓለም አቀፉ የኢነርጂ ዘርፍ የተለቀቀው የልቀት መጠን ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ዘገባው አንስቷል።

የታዳሽ ኃይል አቅምን በሶስት እጥፍ ማሳደግና የኃይል አጠቃቀምን ለመቀነስ የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ማሳደግ በአሥር ዓመታት መጨረሻ የዓለም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በ10 ቢሊየን ሜትሪክ ቶን ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው ጋር ሲነጻጸር መሆኑን ሪፖርቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም