ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የቡና ኩባንያ ስትራውስ ኮፊ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2017(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የቡና ኩባንያ ስትራውስ ኮፊ ልዑክ በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ አስታወቀ።

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ከኩባንያው የእስራኤል ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ መንግስት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለኢንቨስትመንትና ለንግዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኩባንያው በኢትዮጵያ እያደረገ ላለው የንግድ እንቅስቃሴና ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጣው የኩባንያው ልዑክ በሀገር ቤት ለሚያደርገው ጉብኝት ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኩባንያው የእስራኤል ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚያስመጡት የቡና መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የስትራውስ ኮፊ ኩባንያ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያካሂድ መግለጻቸውን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዓለም አቀፉ የቡና ኩባንያ ስትራውስ ኮፊ እ.አ.አ በ1930ዎቹ መጀመሪያ የተቋቋመ ሲሆን በዓለም ላይ ከሚገኙ ምርጥ 10 የቡና ኩባንያዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም